ቴክ

በአገልግሎት አሰጣጥ እምርታ ለማምጣት እየሰራን እንገኛለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Adimasu Aragawu

December 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደ ሌሎች የልማት ስራዎቻችን ሁሉ በአገልግሎት አሰጣጥም እምርታ ለማምጣት እየሰራን እንገኛለን አሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስትቲትዩት የለማ የተቀናጀ የሲቪል ምዝገባ ስርዓት ይፋ አድርጓል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከንቲባዋ እንዳሉት÷ ስርዓቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከተማዋን የሚመጥን አገልግሎት በመስጠት የነዋሪውን እንግልት ያስቀራል።

ስርዓቱ አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ የሚያዘምን መሆኑን ገልጸው፤ ባለጉዳዮች የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም ባሉበት ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

የግዴታ ፎርም መሙላትን የሚያስቀር፣ በኢምግሬሽን፣ በጤና፣ በፍርድ ቤት፣ በብሔራዊ መታወቂያ እና በሎሎችም በተቋማት መካከል ቅንጅት እና መናበብን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የመታወቂያ አሰጣጥ ላይ ያለ ፋይሉ ባለቤት ይሁንታ መታወቂያ እንዳይሰጥ መቆጣጠር የሚያስችል እና ሌሎችም በርካታ ዝርዝር አገልግሎቶችን ማጣመሩንም ጠቁመዋል።

ስርዓቱ ብልሹ አሰራርን በመከላከልና ግልጽነትን በማምጣት ረገድ የጀመርነውን ሰፊ ስራ ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂውን በአጭር ጊዜ ላበለፀገው ለኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምስጋና አቅርበዋል።

በጀማል አህመድ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook WMCC Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!