የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥታችን ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Mikias Ayele

December 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ መንግሥታችን ሕዝብን ያዳምጣል፤ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል አሉ፡፡

በመዲናዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

ውይይቱን አስመልክቶ ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በውይይቱ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ባለሀብቶችና ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል ብለዋል።

በውይይቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሕዝብ መድረኮች ለተነሱ ጥያቄዎች፣ ቅሬታዎች እና አስተያየቶች በተግባር የተሰጡ ምላሾች እንዲሁም ቀሪ ሥራዎችን አስመልክቶ ውይይት መካሄዱን ገልፀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደራችን ከፍተኛ አመራሮችና ሚኒስትሮች መድረኮቹን በመምራት ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ የቤት ስራም ወስደዋል ነው ያሉት።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የልማት ሥራዎች አስደናቂ ስኬቶች የተመዘገቡት መንግሥትና ሕዝብ በቅንጅት በመስራታቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ዛሬም በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር የተሰሩ በርካታ ሥራዎችን እና የተመዘገቡ ውጤቶችን ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም የሕዝብን ተሳትፎ ይበልጥ በሚያረጋግጡ ቀጣይ የጋራ ዕቅዶች ላይ እንደ ወትሮው ከነዋሪዎቻችን ጠቃሚ ግብዓት ያገኘንበት ፍሬያማ መድረክ ነበር ብለዋል።

በውይይቱ ለተሳተፉ፣ ገንቢ አስተያየታቸውን እና ጊዜያቸውን ለሰጡ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበው÷ በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ከህዝቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡