የሀገር ውስጥ ዜና

የዜጎችን ኑሮ መቀየር በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

December 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዜጎችን ኑሮ መቀየር በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል አሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፡፡

“የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሀሳብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የውይይቱ ተሳታፊዎች በከተማዋ የሚታዩ ለውጦች  እየተሰሩ እንደሆነ አንስተው፤ አመራሩ ህብረተሰቡ ጋር ወርዶ ለመስራት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

ወሳኝ የመሰረተ ልማት ችግሮች ተዳራሽ እንዲሆኑ ጥያቄ ያቀረቡት ተሳታፊዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የውሃ አቅርቦት ተደራሽነት እንዲሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ እንዲስተካከል እንዲሁም እየተስተዋለ ያለው ህገ ወጥ የህፃናት ዝውውር ላይ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል፣ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ፣ የኑሮ ውድነት እንዲስተካከል በህዝባዊ ውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሱ ነጥቦች ናቸው።

መንግስት እና ህዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ በትብብር መስራት እንዳለባቸው፣ ሴቶችና ወጣቶች ላይ እንዲሁም በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ መገንባት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ተነስቷል፡፡

በመድረኩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ  ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር)፤ የሃይል መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት የኤሌክትሪክ አቅርቦት መሠረተ ልማት እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል።

የተገልጋይ እንግልትን መቀነስ የሚችሉ ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ መደረጉንም አንስተዋል።

የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በከተማ አስተዳደሩ ባሉ የገበያ ማዕከላት ሻጭናና ሸማች የሚገናኝበት ሂደት እንደተፈጠረም ጠቁመዋል።

የትምህርት ተደራሽነት ችግር የነበረባቸው አካባቢዎች ላይ የተገነቡ 46 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ስራ ማሳያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ÷ ለሰላም እድል መስጠትና የተሳሳቱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ያለው ሰላም በአንፃራዊነት እየተሻሻለ መምጣቱን  አመላክተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ አቅም ያልተነካ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ የዜጎችን ኑሮ መቀየር በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በየሻምበል ምህረት