አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማሊ ጦር ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ቡባካር ኬዬታን በቁጥጥር ስር በማዋል የሀገሪቱን ስልጣን መያዙን አወገዘ።
የማሊ ጦር ባሳለፍነው ማክሰኞ በመንግሥት ላይ ያመፁ ወታደሮች ፐሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬይታ እና ጠቅላይ ሚኒሰትር ባውባው ሲሴን ጨምሮ የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም በርካታ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተግባሩን እያወገዙ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ተቋማቱን በመቀላቀል የማሊ ወታደሮች ተግባርን አውግዟል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሁሉም የመንግስት ባለስልጣናት በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርቧል።
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) አባል ሀገራት መሪዎችም በወቅታዊ የማሊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባን በማድረግ ላይ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ ኢኮዋስ በትናንትናው እለትም ወታደራዊ አመጹን ማውገዙ ይታወሳል።
የአፍሪካ ህብረት፣ ፈረንሳይ እና የአካባቢው ሀገራትም የማሊ ወታደሮችን እርምጃ እንደሚያወግዙ ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።