የሀገር ውስጥ ዜና

በወንድማማች ዓይን ተያይተን በመደመር ዕሳቤ የበለጸገች ሀገርን ለልጆቻችን እናሻግር – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

December 08, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ያንዳችን የሌላችን ውበት፣ ያንዳችን የሌላችን ክብር የሆነባትን ሀገር ኢትዮጵያ አንዱ ከፍ ሌላው ዝቅ ብሎ ሳይሆን ሁላችንም እኩል ሆነን በወንድማማች ዓይን ተያይተን በመደመር ዕሳቤ የበለጸገች ሀገርን ለልጆቻችን እናሻግር አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች በተገኙበት በሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሕብር ቀለም የሚሳል፣ በሕብር ባሕል የሚኖር፣ በሕብር ቋንቋ የሚነገር፣ በሕብር ደም የተሰራ፣ በሕብር ላብ የሚገነባ፣ በሕብር ጥበብ የሚሻገር ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ የነበሩ፣ የሚኖሩ፣ የሚጸኑና የማይናወጡ ናቸው ብለዋል።

በአባቶቻችን ደም የወረስነውን ነፃነት በብልጽግና ማጽናት ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ዛሬ ከተሞቻችን እያሸበረቁ ገጠር መንደሮቻችን ለመሻገር ደፋ ቀና እያሉ፣ ታሪካዊ ቅርሶቻችን አቧራቸውን አራግፈው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ኩራት መሆናቸውን በገሃድ እያሳዩ ናቸው ብለዋል።

መሬትን ክረምት ከበጋ በማረስ ከምግብ ጥገኝነት ለመላቀቅ መላው ኢትዮጵያ በተለይም አርሶ አደሮች እየተጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕድን ሀብታችን እየተገለጠ፣ የቱሪዝም ሀብቶቻችን እያበቡ፣ ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅም እየሰፋና ልምምዱ እያደገ ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛ ከጨለማ ወደ ንጋት እየተሸጋገረች ትገኛለችም ነው ያሉት።

በዚህም የተጀመረውን ለመጨረስ ያልተጀመረውን ለመጀመር ኢትዮጵያን ለማጽናት በጋራ መቆም እንደሚገባ በመግለጽ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook WMCC Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!