ቴክ

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነው – ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ

By Abiy Getahun

December 08, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት መርሃ ግብር ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነው አሉ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ፡፡

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ልማት መርሃ ግብር እና የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ሥራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ በመድረኩ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት የኃይል ደህንነትን በማረጋገጥ የኢኮኖሚያዊ ሽግግርና የረጅም ጊዜ የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ የልማት ተነሳሽነት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂም ንጹህ የኃይል አቅርቦት የማመንጨት አቅምን በማላቅ የጤና፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ እንዲሁም የምርምር ትግበራ ማዕቀፍ የተቃኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰላማዊ አማራጭ የኒውክሌር ሳይንስ ልማት መርሃ ግብሩም የኢትዮጵያውያንን ህይወት በተጨባጭ የሚያሻሽሉ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ዕድል ማረጋገጥ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኒውክሌር ኃይል ልማት ቁርጠኝነትም ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ መሆኑን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ በጉባ ከመበሰሩ ማግስት በሩሲያ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል መድረክ ድረስ ኢትዮጵያ ለሰላማዊ የኒውክሌር ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ለመጠቀም ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ነች ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን በተሰጠው ግልጽ ሥልጣንና በተፈጠረለት ጠንካራ መዋቅር ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ በዕውቀትና በሰላማዊ የኒውክሌር ልማት የጋራ ርዕይ በመመስረት ከዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የትብብር ስራን አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook WMCC Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!