አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለኢትዮጵያ ኩባንያዎች የፋይናንስ ተደራሽነትን ማሻሻል የሚያስችል የንግድና የፋይናንስ መድረክ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ከ250 በላይ የፋይናንስ ተቋማት ማለትም የባንክ፣ የኢንቨስትመንት እና ሌሎች የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ይታደማሉ፡፡
መድረኩ በባንኮች፣ በኢንቨስተሮች እና በካፒታል ገበያ ተቋማት መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትስስርና ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
የፋይናንስ ተቋማት በአንድ ቦታ ተገናኝትው ያላቸውን ተሞክሮ እንዲጋሩ ከማስቻሉ ባለፈ የንግድ ትስስርና አጋርነት እንዲፈጥሩ ሚናው ጉልህ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
መርሐ ግብሩ ለኢትዮጵያ ኩባንያዎች የፋይናንስ ተደራሽነትን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ወጪ ንግድን ለማሳለጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ በግሉ ዘርፍ የሚስተዋሉ የሥራ ካፒታል፣ የንግድ ፋይናንስ፣ ረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንት ገንዘብ እና የሪስክ መጋራት ተግዳሮቶችን ለመቀነስ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ ከ20 በላይ የፋይናንስ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸው በማቅረብ የንግድ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩ ይሆናል፡፡
የንግድና የፋይናንስ መድረኩን ጂአይ ዜድ ኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ አጋሮች (ኢኤፒ) ኮንሳልቲንግ እንዲሁም ካፌ ፈርም ፋይናንስ ኢትዮጵያ በጋራ እንደሚያዘጋጁት ይጠበቃል፡፡