አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ ገዢ ትርክትን ይበልጥ ለማስረጽ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር።
አፈ ጉባዔ አገኘሁ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያዊነት የሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መገለጫና እኩል የሚሳተፉበት ማንነታቸው ነው።
ኢትዮጵያዊነት ስንፈልግ የምንለብሰው ፤ሳንፈልግ ደግሞ አውልቀን የምንጥለው ማንነት ሳይሆን በደማችን እየኖረ ያለ እና የሚኖር የሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ ነው ብለዋል።
አሁን ያለው ችግር ጽንፍ የያዙ አመለካከቶች ውጤት መሆኑን ገልጸው ÷ ችግሩን ለማረቅና ለማስተካከል በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ብሔራዊ ትርክት ለማስረጽ እየተሰራ ነው ያሉት አፈ ጉባዔው ÷ የሀገራዊ ለውጡ ዋነኛ መለኪያ እና እሳቤም ይሄው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያውያንን ከሚለያዩዋቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው ጉዳዮች እንደሚበልጡ አውስተው ÷ ለዚህም የኢትዮጵያውያን የድል ውጤት የሆኑትን የዓድዋ ድልን እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንደ አብነት አንስተዋል።
በጋራ የምንቆምባቸውና የሚያደምቁን የበርካታ ታሪክ ባለቤት ሕዝቦች ነን ያሉት አፈ ጉባዔው ÷ ኢትዮጵያውያንን ለመነጣጠል በርካታ ጊዜያቶች ተሞክረው ሳይሳኩ መቅረታቸውን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የነጠላ ትርክትን ማራመድ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ አድርጎ ማሰብ በስፋት እንደሚስተዋል አመልክተዋል፡፡
የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠርና በጉልበት ስልጣን ማግኘት እንደማይቻል የገለጹት አፈ ጉባዔው ÷ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ ስልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በትጥቅ ትግል መንግስትን መቀየር አይቻልም፤ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ እነዚህን ጥያቄዎች በጠረጴዛ ዙሪያ አንስቶ መነጋገር ይቻላል ፤ነገር ግን በክላሽ መልስ ማሰጠት አይቻልም ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም የፖለቲካ ምሁራን ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው ÷ ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ በኃይል ስልጣንን መቆጣጠር አይቻልም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት