የሀገር ውስጥ ዜና

የተጀመሩ መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Adimasu Aragawu

December 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ ዛሬ ማለዳ ከኡራኤል ብራስ፣ ቦሌ መድኃኒዓለም ጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የፒኮክ (ማዕከላዊ) ፓርክ ግንባታን ገምግመናል ብለዋል።

ይህ ኮሪደር በከተማችን በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትን ለማስፋት የተጀመረ ዘጠነኛው ኮሪደር ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ አጠቃላይ 11 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እና በውስጡ በርካታ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎችን የያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

የግንባታው ሂደትም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከኮሪደሩ በተጨማሪ ለብዙ ዘመናት ተረስቶ የኖረ፣ ከሕዝብ ተወስዶ በግለሰቦች ያለአግባብ ተወሮ ለብዙ ብልሽት ተዳርጎ የኖረውን ታሪካዊውን የፒኮክ ወይም በጥንታዊ መጠሪያ ስሙ ማዕከላዊ ፓርክን ከወንዝ ዳርቻ ጋር አያይዘን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያለማነው ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ሌላኛው የስበት ማዕከል፣ ድንቅና ውብ ስፍራ ሆኖ እየተገነባ ነው ብለዋል።

በተለይም የኮፕ32 ጉባኤ በሚከናወንበት በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ አስቀድመው የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመላክተዋል።

በዚህም የኮፕ32 ጉባኤ ከዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የሚታደሙበት በመሆኑ ጉባኤው በመዲናዋ መዘጋጀቱ ከሀገር መልካም ገፅታ ግንባታ በተጨማሪ፤ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ትስስር እንዲሁም መሰል ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ወደ ሀገራችን በቀጣይነት ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ የሚፈጥር ስለሆነ ከመቼውም የበለጠ ትኩረት ይሻል ነው ያሉት።

በመሆኑም መላው የከተማዋ ነዋሪዎችና የንግዱ ማሕበረሰብ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጉባኤው ይዞት የሚመጣውን መልካም ዕድል አሟጦ እንድንጠቀም እና ለጉባኤው ስኬታማነትም ከወዲሁ ሁላችንም ዝግጅት እንድናደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook WMCC Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!