የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቀድሞ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በ13 ዓመት እስራት ተቀጡ

By Mikias Ayele

December 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቀድሞ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በ13 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ በኮሚሽኑ የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን የተለያዩ የእርዳታ ዓይነቶችን ከመጋዘን ወጪ በማድረግ ለተረጂዎች ሳይደርስ ተሽጦ ለግል ጥቅም መዋሉን አስረድቷል፡፡

በዚህም የሙስና ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 3 የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እንዲሁም 33 እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ምንጩን ደብቆ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም ተመስርቶባቸው ነበር፡፡

አቶ ምትኩ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያምና ከሌሎች ሰራተኞች ጋር ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር በሺዎች በሚቆጠሩ ተረጂዎች ስም እንዲሁም የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ለበርካታ ጊዜ የምግብ ቁሳቁሶች ከኮሚሽኑ መጋዘን በማውጣት ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለሌሎች ግለሰቦች በመሸጥ ሕገወጥ ጥቅም ሲያገኙ እንደነበር በክሱ ተመላክቷል፡፡

በዚህም በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልል (የቀድሞ) ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የግብረሰናይ ድርጅቱ ማዕከላት ለተረጂዎች ሳያደርስ በመሸጥ ለግል ጥቅም ማዋል፣ ብድርና ድጋፍ በሚል ሰበብ በሕገ ወጥ መንገድ ከኮሚሽኑ በ100 ሚሊየን የሚገመት ለእርዳታ ድርጅቱ በገንዘብ መልክ መሰጠቱ ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡

ለዚህም በአቶ ምትኩ ካሳ ቤተሰቦች ስም ከኤልሻዳይ ድርጅት በተለያዩ ጊዜ ክፍያ መፈጸሙንም ነው በክሱ የተመላከተው፡፡

በተለይም ከ601 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ፣ ከ41 ሺህ ኩንታል በላይ በቆሎ፣ ከ78 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት፣ 3 ሺህ 999 ኩንታል ሩዝ ከተራድኦ ድርጅቱና ከኮሚሽኑ ጋር በመመሳጠር እርዳታውን አዳማ ለሚገኝ የዱቄት ፋብሪካ መሸጡ ተጠቅሷል።

በ2ኛ ክስ ደግሞ ከ472 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በድጋፍ መልክ በ1ኛ ተከሳሽ አቶ ምትኩ ካሳ ፈቃጅነት በ2ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ክፍያ እንደተፈጸመና በ3ኛ ተከሳሽ ወጪ አድራጊነት ለግል ጥቅም በመዋሉ በመንግስት ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰ መሆኑ ተገልጿል።

በአቶ ምትኩ ልጆችና ባለቤታቸው ስም ተገዝተው የተገኙ ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው በክሱ የተጠቀሰ ሲሆን ፥ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በሌሎችም ተከሳሾች ላይ በየደረጃው የወንጀል ተሳትፏቸው በክሱ ተዘርዝሮ ተካትቷል።

ተከሳሾቹ አቶ ምትኩ ካሳ፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል፣ ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ የወንጀል ድርጊት መፈፀማቸውን ተከትሎ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት የዐቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃና የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያ ካደመጠ በኋላ አቶ ምትኩ ካሳ በ13 አዓት ጽኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

በተጨማሪም በአቶ ምትኩ ካሳ ባለቤት ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል ላይ የ8 ዓመት ከ4 ወር እስራትና  3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲሁም ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ 5 ዓመት እስራትና 3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።

በሲፈን መኮንን