አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የሚከናወነውን የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታ አስጀምሯል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ የፕሮጀክቱን የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የፌዴራል መንግስት በመጠጥ ውሃ፣ በውሃ ሃብት አስተዳደርና በኢነርጂ ሁሉንም ማህበረሰብ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ በከተሞች የፍሳሽ አወጋገድ እንዲሁም ፍሳሹን በማከም ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ በትግራይ ክልል ከ8 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በመቀሌ ከተማ የተጀመረው ፕሮጀክት በሀገራችን በአምስት ከተሞች ላይ መንግስት የሚተገብረው የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን፥ ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር እንደሚሸፈን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተለይ ወጣቶችን ወደ ስራ በማስገባት በግንባታ ግብአት አቅርቦት የሚያሳትፍ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ፕሮጀክቱ በ18 ወራት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ገልጸው፥ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
ግንባታው በአሰር ኮንስትራክሽን እንዲሁም የማማከር ስራው በሃይድሮ ፕላን እንደሚከናወን የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ጌትነት ስሜ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ