አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” የወላይታ ብሔር ለዘመናት ሲያከብረው የኖረ ደማቅ ባህላዊ እሴት ነው፡፡
ጊፋታ የተጣላና የተኮራረፈ የሚታረቅበት እንዲሁም የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት ይበልጥ የሚጠናከርበት የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
የባሕል፣ታሪክና ቅርስ ባለሙያ የሆኑት አዳነ አይዛ እንደሚሉት÷ ጊፋታ ታላቅ፣ በኩር፣ የመጀመሪያ፣ መሻገር የሚል ትርጓሜ አለው ፤ ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገርን የሚያሳይ ነው።
ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ይህ የዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታ በወላይታ ባሕላዊ የጊዜ አቆጣጠር የመጀመሪያው ወር መሆኑን ያብራራሉ፡፡
መርሐ ግብሩ የጨረቃን እንቅስቃሴን መሰረት ያደረገው የወላይታ ብሔር ባሕላዊ የጊዜ አቆጣጠርን በመከተል የሚከበር መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
ረጅም የሆነ የዝግጅት ጊዜን የሚወስደው የጊፋታ በዓል ከአባቶች ጀምሮ እስከ ሕጻናት ድረስ በጊፋታ በዓል ዝግጅት የየራሳቸው የሥራ ድርሻ ያላቸው ሲሆን ÷ የቅድመ ዝግጅት ሥራው በአብዛኛው በደቦ ይከወናል።
በዓሉ በሚቃረብበት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል እርቅ ዋናው መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው÷ በዚህ ወቅት የተጣሉ ሰዎች እርስ በርሳቸው ታርቀው እና ጥላቻን ረስተው የጊፋታ በዓል እንደሚያከበሩ አውስተዋል፡፡
የተበደሩትን ዕዳ መክፈል ሌላኛው የጊፋታ በዓል ቅድመ ዝግጅ እንደሆነ እና ዕዳን ሳይከፍሉ ጊፋታን ማለፍ የተወገዘ ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በሰኔ ወይም “ጉልያ” ወር ላይ ወጣቶች ተሰባስበው ወደ ጫካ በመሄድ የአካባቢውን ደን በማይጎዳ መልኩ እንጨት ቆርጠው በማምጣት በአንድ ቦታ ላይ በማከማቸት በዓሉን በእሳት ብርሃን ለማክበር ይሰናዳሉ፡፡
እንዲሁም በዓሉ ሲቃረብ የመታደስ ምልክት የሆነውን በዓል ከመድረሱ በፊት አካባቢያቸውን የማጽዳት ሥራ የሚያከናውኑ ሲሆን÷ የጎጆ ቤታቸውን ሳር በአዲስ የመቀየርና የተለያዩ ያረጁ አላስፈላጊ ቁሶችን የማስወገድ ሥራ ያከናውናሉ፡፡
የባህል ታሪክ እና ቅርስ ባለሙያ የሆኑት ግርማ ገነነ በበኩላቸው÷ በዓሉ ከሁለት ወር በላይ የሚሆን ጊዜ ሲቀረው አባዎራዎች ለእርድ ቀን ቁመት ያለው በሬ በመግዛት ለተመረጠ የቤተሰብ እንደሚያስረክቡ እና የተረከበው ቤተሰብ እንዲወፍር እና ስጋውም ጣፋጭ እንዲሆን በደረቅ የኮባ ቅጠል በተሸፈነ ልዩ ጋጣ ተቀምጦ እንደሚቀለብ ያብራራሉ።
በጊፋታ በዓል ዝግጅት አባቶች አና ታላላቅ ወንድ ልጆች የጉሊያ እንጨት መቁረጥ፣ ማቆምና ማቃጠል የማገዶ እንጨት መፍለጥ፣ የቆጮ መቁረጥ እና ሌሎች ስራዎችን ያከናውናሉ፡፡
እናቶች እና ሴት ልጆቻችው ደግሞ ለተለያዩ ባህላዊ ምግቦች እንሰቶችን መፋቅ፣ የማሽላና በቆሎ ዱቄት፤ ዳጣ በርበሬ የማዘጋጀት፣ የተለያዩ ባህላዊ መጠጦችን እንደ ቦርዴ፣ ጠላ እና ወተት በትላልቅ እንስራ ያዘጋጃሉ።
የጊፋታ በዓል የሚከበርበት የአዲሱ ዘመን የመጀመሪያ ቀን ከሆነው እና እርድ ከሚከናወንበት የእሑድ ቀን በፊት ቅዳሜ ላይ ሁሉም ሰው ንጽሕናውን የመጠበቅ ሥራ ያከናውናል፡፡ ይህ የሚደረገውም ከአሮጌው ዓመት እድፍና ቆሻሻ ጋር ወደ አዲሱ ዓመት መሻገር አያስፈልግም በሚል ነው ፡፡
የዕርድ ዕለት እሑድ ጠዋት ወፍ እንደተንጫጫ የበሬ አራጆች ሥራቸውን ይጀምራሉ፤ በዚሁ ወቅትም እናቶች ያዘጋጁት መጠጥ እና ምግብ በእርዱ ለሚሳተፉት ይቀርባል።
አባወራዎች ስጋውን ተከፋፍለው ወደ ቤታቸው ከመውሰዳቸው በፊት ሁሉም በአንድ ላይ ይበላሉ ይጠጣሉ፤ ይህም ፍቅራቸውን ከአንድ ማዕድ በመቁረስ የሚያድሱበትና የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ የሚያበስሩበት እንደሆነ ግርማ ገነነ ያብራራሉ።
በቀጣይ ዕጣ በመጣጣል ሥጋውን ተከፋፍለው ለጊፋታ ተብሎ በሚገዛ አዲስ ቅርጫ ስጋውን ይዘው ወደ ቤታቸው እንደሚወስዱ እና እናቶች በቤት ውስጥ የመጣውን ስጋ ባልተበሳሳ ኮባ ቅጠል ላይ ዙሪያውን በማስቀመጥ በቆጮ፣ በቂጣ፣ በዳጣ በርበሬ ተደርጎ እንደሚቀመጥና አባት ማዕዱን እናትን በማጉረስ እንደሚጀምሩ ያስረዳሉ።
በሰኔ ወር በወጣቶች የተሰበሰበው እንጨት (ጉሊያ) ለጊፋታ በዓል ሁለት ሳምንት ሲቀረው እንዲቆም የሚደረግ ሲሆን÷ በዕለቱ አመሻሽ ላይ ሁሉም በተሰበሰበበት አባወራ ጉሊያውን በእሳት ይለኮሳል፡፡
ወጣቶችም ዞሪያውን በመክበብ ባህላዊ ጭፈራ ይጨፍራሉ፤ በቀጣዩ ቀንም በቤት ውስጥ የተረፈው ሥጋ ተዘልዝሎ ይጠበስና ማባያ ተዘጋጅቶ ሁሉም ተሰብስበው በመመገብና በመዝናናት በአንድነት ያሳልፋሉ።
ከጊፋታ ቀጥሎ የሚመጣው ሁለተኛው ቀን ደግሞ በጊፋታ ወቅት ብቻ የሚፈካን ነጭ አበባ ይዞ በመሄድ ዘመድ የሚጠያየቅበት ዕለት ሲሆን÷ አበባውን የሚቀበሉት አባዎራ ከምሶሶ ጋር በማሰር በጋራ በልተው እና ጠጥተው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።
ከጊፋታ ከሦስተኛው ቀን ጀምሮ ደግሞ በተከታታይ ለሁለት ሳምንታት ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች በአካባቢው ታዋቂ ሽማግሌ ደጃፍ ተሰብስበው በመዝፈንና በመጫወት ያሳልፋሉ፡፡
ይህም ጋዜ ኦሩዋ በመባል ይታወቃል። ለረጅም ጊዜ የቆየው የበዓል ዝግጅትና አጠቃላይ የጊፋታ በዓል ሥነ ሥርዓት የጋዜ ኦሩዋ ጨዋታ ሲጠናቀቅ ችቦ በማቀጣጠል ለሚመጣው በዓል በሰላም እንዲያደርሳቸው በመመኘት ነው የሚጠናቀቀው።
ይህ የወላይታ ሕዝብ የአዲስ ዓመት ፌስቲቫል በ2ዐኛው የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ ጥበቃ የመንግስታት ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት በተባበሩት መንግስታት ትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቧል።
በዓሉ እድሜ፣ ጾታ፣ ሐይማኖትና ማህበራዊ ደረጃን ሳይለይ የሚያሳትፍ መሆኑ፣ የቅርሱ ተስተላልፎ ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም በት/ቤቶችና በሚዲያዎች ለትውልድ በመሸጋገር ላይ የሚገኝ መሆኑ እና ሌሎች መመዘኛዎችን በማሟላቱ ነው በዩኔስኮ መመዝገብ የቻለው።
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!