ጤና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖሊዮ ክትባት ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ ይሰጣል

By Hailemaryam Tegegn

December 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 4ኛው ዙር ክልላዊ የፖሊዮ ክትባት ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ በዘመቻ መልክ ይሰጣል አለ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አጉኔ አሾሌ እንዳሉት ÷ ክትባቱ ከታሕሳስ 3 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ነው በዘመቻ መልክ የሚሰጠው፡፡

ቤት ለቤት የሚሰጠውን ክትባት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት እንደሚወስዱ አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ የሥርዓተ ምግብ ጉድለት ያለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶችን እንዲሁም ቆልማማ እግር ያላቸው ሕጻናትን በመለየት ነጻ ሕክምና ወደሚሰጥባቸው ጤና ተቋማት የመላክ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የማርበርግ ቫይረስ ምልክት የሚታይባቸው ሰዎችን በመለየት ወደ ሕክምና ማዕከላት የመላክ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለክትባት ዘመቻው የሚያስፈልገው ዝግጅት መጠናቀቁንና በዘመቻው ለሚሳተፉ ባለሙያዎች በቂ ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።

በመለሰ ታደለ