አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የኢንስቲትዩቱ ሥራ መጀመር ዘመናዊና አስተማማኝ የፋይናንስ ሥርዓት በመገንባት ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና አለው፡፡
ለፋይናንስ ሥርዓቱ የጀርባ አጥንት ከመሆን ባለፈ አስተማማኝ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲፈጠር፣ ሕብረተሰቡ ስለፋይናንስ ዘርፉ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ለውሳኔ ሰጪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በተለይም የኢኮኖሚ ዕድገት እና ሽግግርን በማሳለጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ በቂ የተመሰከረላቸውየሒሳብ ባለሞያዎች አለመኖር በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ የሒሳብ ሥራዎች ግልጽነት የጎደላቸው መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ሥራ መጀመርም በዘርፉ ያለውን ችግር አጥርቶ ለመመልከት እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
በመድረኩ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ፣ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የዓለም ባንክ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በቅድስት ተስፋዬ