ስፓርት

ስሞት አንፊልድ ወስዳችሁ ቅበሩኝ – ስቴቨን ጀራርድ

By Yonas Getnet

December 12, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሊቨርፑላውያን እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚወዱት ታማኙ ልጃቸው ነው ስቴቨን ጀራርድ፡፡

እንግሊዛዊው የሊቨርፑል የቀድሞ ተጫዋች ስቴቨን ጀራርድ ከምን ጊዜም ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡

በመርሲሳይድ ጎዳና ሲጫወት ያደገው ጀራርድ ገና በማለዳ ጓደኞቹን ቀድሞ ነበር መጫወቻ ቦታ የሚደርሰው፡፡

የጀራርድ ቤተሰቦች በእግር ኳስ ፍቅር ያበደውን ልጃቸውን ከመደገፍ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ያቀርቡለት ነበር፡፡

ስቴቨን ጀራርድ በታዳጊነቱ እኔ በዚህ ዓለም ስፈጠር ቀዩን ማልያ ለብሼ ሊቨርፑልን ለማገልገል ነው ሲል ለወላጆቹ እየተናገረ ያደገ ድንቅ ኮከብ ነው፡፡

ታላቁ ኮከብ ስቴቨን ጀራርድ ገና በታዳጊነቱ ለቤተሰቦቹ ስሞት ወደ ሌላ መቃብር ስፍራ እንዳትወስዱኝ አንፊልድ ወስዳችሁ ቅበሩኝ በማለት ለሊቨርፑል ያለውን ልዩ ፍቅር ገልጿል።

የታማኝነት ተምሳሌቱ ጀራርድ በታዳጊነቱ ያልመው የነበረው ነገር ተሳክቶለት ከፈረንጆቹ 1998/99 ጀምሮ የሊቨርፑል ዋናውን ቡድን በመቀላቀል በቀዩ ማልያ እስከ 2014/15 የውድድር ዓመት ድረስ ተጫውቷል፡፡

በሊቨርፑል ቆይታው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ፣ ኮሚኒቲ ሺልድ እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

በተለይም ሊቨርፑል በ2004/5 የውድድር ዓመት በፍጻሜው ኤሲሚላንን አሸንፎ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ሲያሳካ ጀራርድ ትልቁን አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይዘነጋም፡፡

ኢስታንቡል አታቱርክ ኦሎምፒክ ስታዲየም በ69 ሺህ ደጋፊዎች ፊት በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ሊቨርፑል በሚላን 3 ለ 0 እየተመራ የመጀመሪያውን አጋማሽ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የሊቨርፑል ልዑል የሆነው ጀራርድ 54ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሮ የመርሲሳይዱን ክለብ ወደ ጨዋታው መመለስ የቻለ ሲሆን÷ ሊቨርፑሎች ተጨማሪ ሁለት ግብ አስቆጥረው አቻ በመሆን መደበኛ የጨዋታ ጊዜው ተጠናቅቋል፡፡

በመጨረሻም በአሰልጣኝ ራፋኤል ቤኒቴዝ የሚመሩት ሊቨርፑሎች በመለያ ምት ሚላንን አሸንፈው ዋንጫውን አሳክተዋል፡፡

በጨዋታው ሊቨርፑልን በአምበልነት የመራው እና ቡድኑን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ ያስቆጠረው ስቴቨን ጀራርድ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ መመረጡ ይታወሳል፡፡

ጀራርድ በልጅነቱ ወደ ማንቼስተር ዩናይትድ የልምምድ ማዕከል ለሙከራ ቢሄድም ማንቼስተር ዩናይትድን አጥብቆ እንደሚጠላ ተናግሯል፡፡

በእሱ ሕይወት ዙሪያ በተሰራው ዶክመንተሪ ፊልም ላይ ከጨዋታ በኋላ ከተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ጋር የተቀያየራቸውን ማልያዎች ሲያስጎበኝ ይታያል፡፡

የምትመለከቷቸው ማልያዎች ከጨዋታ በኋላ የተቀያየርኳቸው ናቸው፤ አንድም የማንቼስተር ዩናይትድ ማልያ መደርደሪያዬ ላይ የለም ምክንያቱም ማንቼስተር ዩናይትዶችን አጥብቄ ነው የምጠላቸው ሲል ተናግሯል፡፡

ለሊቨርፑል ታምኖ ለበርካታ ዓመታት በቀዩ ቤት ደምቆ የቆየው ጀራርድ በሊቨርፑል ደጋፊዎች ልዑላችን እየተባለ የሚዘመርለት አይተኬ ኮከባቸው ነው፡፡

የእንግሊዝ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ለ14 ዓመታት ያገለገለው ስቴቨን ጀራርድ ለብሔራዊ ቡድኑ 114 ጨዋታዎችን አድርጎ 21 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡

ወደ አሰልጣኝነት ከገባ በኋላ ሬንጀርስ፣ አስቶንቪላ እና አል ኢቲፋቅን ማሰልጠኑ ይታወቃል፡፡

ሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎትን የሚያሰናብት ከሆነ ሊቨርፑልን ይረከባሉ ተብለው ከሚጠበቁ አሰልጣኞች መካከል ስቴቨን ጀራርድ አንዱ ነው፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation

Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting

Facebook https://web.facebook.com/fanasport

Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate

Telegram t.me/fanatelevision

Website www.fanamc.com

TikTok www.tiktok.com/@fana_television

WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29

Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment

TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment

Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!