አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ መፍጠን፣ መፍጠር፣ ማብዛት እና ማጥራት የሚሉ ወሳኝ መንገዶችን ይከተላል።
የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንደሚሉት፥ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እነዚህ አራት መንገዶች እርስ በእርስ የተያያዙና ለብቻ ተነጥለው ሊተገበሩ የማይቻሉ ናቸው።
መፍጠን የሚለው መንገድ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም እንደሚስተዋለው የሚባክን ጊዜ ሳይኖር የተጀመሩ የልማት ስራዎችና ፕሮጀክቶች በፍጥነት መጠናቀቅ አለባቸው የሚለውን አቅጣጫ የሚገልጽ መሆኑን አብራርተዋል።
ያደጉ ሀገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ እነሱ የፈጀባቸውን ያህል ጊዜ መጠበቅ እንደማይገባ ገልጸው፥ አንድ አመትን እንደ አምስት አመት እንዲሁም አምስት አመትን እንደ 25 አመት እንጠቀመዋለን ነው ያሉት።
የኮሪደር ልማት፣ የተጠናቀቁ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት የመስራትን ውጤታማነት ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመቀጠልም መንግስት ያሉንን ሀብቶች በመመልከት የራስ እውቀትና ክህሎትን በመጨመር አዲስ ነገር ማፍለቅ በሚል መፍጠር የሚለውን ሁለተኛውን መንገድ እንደሚከተል አስረድተዋል።
ግብርና፣ ኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች የምናብ ከፍታችንን በማሳደግ አዲስ ነገሮችን በመፍጠር አምራችትን ማሳደግ እንደሚገባ አመላካች መንገድ ነው ብለዋል።
ኃላፊው ሦስተኛው መንገድ ማብዛት መሆኑንና ይህም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ አመራረትን በማስቀረት ከራስ ፍጆታ በዘለለ ለዓለም ገበያ ምርቶችን በብዛት ማቅረብ የሚል እሳቤ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህንን መንገድ በመከተል በግብርናው ዘርፍ የክረምት ዝናብን በመጠበቅ ብቻ ምርትን የማምረት ልምድን በመቀየር የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በመጀመር በብዛት ማምረት መቻሉን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም በዲጂታል ዘርፉም በአንድ ጊዜ 5 ሚሊየን ኮደርስ በማሰልጠን ረገድ የተገኘው ውጤትም የዚህ መንገድ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማብዛት የሚለው ሦስተኛው መንገድ ትንሽ ትንሽ ከመስራት ይልቅ ብዛት ያለው ምርት በማምረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ላይ ያተኮረ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
ማጥራት የሚለው የመደመር መንግስት መንገድ የሚሰሩ ስራዎችም ሆነ ምርቶች ተገቢው ጥራት ሊኖራቸው ይገባል የሚል ሀሳብ የያዘ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተወዳዳሪነት ሊረጋገጥ የሚችለው ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ዓለም አቀፍ የጥራት መለኪያ ማሟላት ሲችሉ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ምርቶችን በፍጥነት ብቻ ሳይሆን ፈጠራን በማከል በብዛትና በጥራት ማምረት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ