የሀገር ውስጥ ዜና

የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እድሳት ታሪኩን የተሟላ ያደርገዋል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Hailemaryam Tegegn

December 12, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመዲናዋ የሚገኘው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሕንጻ እድሳት ሥራ የቤተ ክርስቲያኑን ታሪክ የተሟላ ያደርገዋል አሉ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በቤተ ክርስቲያኑ እየተከናወነ የሚገኘውን የሕንጻ እድሳት ሥራ ጎብኝተዋል፡፡

የሕንጻ እድሳት ሥራው ደረጃውን በጠበቀና ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፥ የቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻና ግቢ ታሪካዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መታደሱ ታሪኩን የተሟላ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የሕንጻው የአሠራር ጥበብ፣ የሥዕሎቹ ጥበባዊ ከፍታ፣ የብረት ሥራዎች የዕደ ጥበብና የጥራት ደረጃ እንዲሁም የቅርሶቹ የላቀ ዋጋ እጅግ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል፡፡

ከዓድዋ ድል ጋር በእጅጉ የተሣሠረ ታሪክ ያለው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በ2ኛው የፋሽስት ወረራ ወቅት እንደ ጦር ወንጀለኛ ተቆጥሮ በእሳት እስከ መቃጠልና ጥቁር ቀለም እስከ መቀባት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዚሁ አካባቢ መገንባቱ፣ ለዳግማዊ ምኒልክ ዐደባባይ ጥገና መደረጉና የመመልከቻ አምፊ መሠራቱ የአካባቢውን የቱሪዝም ፍሰት ከፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ማዕከል እያደረገው ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኑና የአካባቢው የእድሳት ሥራዎች ከከተማ ማዘመን፣ ከቱሪስት መዳረሻዎችና የቅርስ አጠባበቅ ደረጃዎች ጋር ተጣጥሞ እንዲሠራ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡