አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል ከቀነገደቡ በፊት አሟልቻለሁ አለ፡፡
የግሎባል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ ባንኩ ዘመኑን የዋጀ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ አስተማማኝና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም የኮር ባንኪንግ ሥርዓትን በመጠቀሞ የዲጂታል ባንኪንግ ማለትም የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ እንዲሁም የአጭር መልዕክት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉን በማሳደግ 5 ቢሊየን ብር ማድረሱን ጠቁመው ÷ በዚህም ባንኮች ካፒታላቸውን 5 ቢሊየን ብር እንዲያደርሱ የተቀመጠውን አቅጣጫ ከጊዜ ገደቡ በፊት ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል፡፡
ባንኩ በ2024/2025 በጀት ዓመት ከ 5 ነጥብ 56 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው÷ ጠቅላላ ሃብቱም ከ 34 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከታክስ፣ ከመጠባበቂያ እና ሌሎች ተቀናሾች በፊት 1 ነጥብ 17 ቢሊየን ብር በላይ ማትረፍ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡
በሌላ በኩል 7 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን ÷ የባንኩን አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ወደ 25 ነጥብ 75 ቢሊየን ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 12 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አሁን ላይ የባንኩ ቅርንጫፎች ብዛት 237 መደረሱን ጠቁመዋል፡፡
አካታች የባንክ አገልግሎትን እና የብድር ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡