አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ላለው ሁሉን አቀፍ ልማት የዜጎቿ ተሳትፎ ከፍተኛ ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፡፡
በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ “የጉባ ብስራቶች ፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሃሳብ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ አቶ አሕመድ ሽዴን ጨምሮ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡
አቶ አሕመድ ሽዴ በመርሐ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት÷በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች ውጤት እየመጣ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና ሌሎች ዘርፎች የሀገሪቱን አቅም እጅጉን የሚያሳድጉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
የሥራ እድልን በመፍጠርና የኑሮ ሁኔታን በማቃለልም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
የማዕድን ልማት ላይ በተሰራ ሥራ ከፍተኛ የማዕድን ግኝት በማምጣት የኤክስፖርት መጠንን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በቴክኖሎጂው ዘርፍም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የቴክኖሎጂ ምንጭ በማድረግና ወጣቱን በስፋት በዘርፉ ላይ በማሰማራት ውጤቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ባላት ሃብት ልክ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል ከፍተኛ የቱሪዝም ልማት ሥራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
በተለይም የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና ይበልጥ ምቹ በማድረግ ሳቢነታቸው እንዲጎላ የተደረገ ሲሆን÷ ይህም በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል።
በከተሞች ልማት የኮሪደር ልማትን በማስፋፋትና ምቹ የሥራ አከባቢን በመፍጠር እንዲሁም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት ሰፊ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ሁሉ ውጤት እንዲመዘገብም የሀገሪቱ ዜጎች ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው ሚኒስትሩ አንስተዋል።
በመድረኩ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሀይሉ ጀልዴ÷ መንግሥት ሁለገብ የለውጥ እሳቤን ለማስመዝገብ ሰፋፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ሀገሪቱ ሉዓላዊነቷ እንዲጠበቅና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት እንዲኖራት አስችሏል ነው ያሉት።
በታምራት ደለሊ