የሀገር ውስጥ ዜና

በሀገራዊ ለውጡ በተግባር እውን የሆነው የአፋር ክልል ህዝብ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት …

By Mikias Ayele

December 14, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአፋር ክልል ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎ እና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነቱ በተግባር እውን ሆኗል አሉ።

‘የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች’ በሚል መሪ ሃሳብ በሰመራ ሎጊያ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

የመድረኩ ተሳታፊ የሰመራ ሎጊያ ነዋሪዎች በክልሉ የመስኖ ልማትን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ በመሆኑ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረት እየተሳካ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በክልሉ የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የልማት ስራዎች ለሀገርም ጭምር የሚጠቅሙ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው የመንግሥት አስተዳደር የክልሉ ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎና የልማት ተጠቃሚነት ፍትሃዊነት የጎደለው እንደነበር አንስተው፤ በለውጡ መንግሥት እኩልነትና ፍትሃዊነት በተግባር ተረጋግጧል ብለዋል።

በክልሉ ወጣቱን ማዕከል ያደረጉ የልማትና የስራ ዕድሎች እየተመቻቹ እንደሆነ በማንሳት፤ ጅምሩን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተለይም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ወንጀልን ለመከላከል ወጣቶችን በጥሩ ስነ ምግባር መቅረጽና በቂ የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ አመላክተው፤ ለውጡን ተከትሎ የክልሉ ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነቱ በተግባር እውን ሆኗል ብለዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ በሁሉም አካባቢዎች የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፋር ክልል የተከናወኑ እና በመከመናወን ላይ ያሉ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን አንስተው፤ የህዝቡ ጥረትና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከግብርና በተጨማሪ በኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና የዲጂታል ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ የጋራ ጥረት ይጠይቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አሳታፊና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የተረጋገጠባት ጠንካራ ሀገር የመገንባት ዓላማ በመሰነቅ በተሰራው ስራ እመርታዊ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።