አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን የተዘጋጀው የመጀመሪያው የከተማዋ የቱሪዝም ፎረም በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
ፎረሙ የዘርፉን ትስስር ለማጠናከር፣ የሆቴልና ቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማነቃቃት እንዲሁም ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በመክፈቻው የቱሪዝም ንግድ ዐውደ ርዕይ እና ኮሚሽኑ ከተማዋን ለማስተዋወቅ ያበለፀጋቸው ዲጂታል ፕላትፎርሞች ይፋ ተደርገዋል።
ይፋ ከተደረጉት ውስጥም ‘ቪዝት አዲስ አበባ’ የተሰኘው ፕላትፎርም በመዲናዋ የሚገኙ መዳረሻ ቦታዎችን ለጎብኚዎች የሚጠቁም ሲሆን ÷አዲስ አበባን ምን ያህል ሰው እንደጎበኛት መረጃ እንደሚሰጥም ተጠቅሷል፡፡
ፕላትፎርሞቹ በከተማዋ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችንና መዳረሻዎችን በሕብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር ብሎም ስፖርት ቱሪዝምን ለማጎልበት ያግዛሉ፡፡
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድርን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።