አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “ችቦው በራ፣ ስታዲየሙ ተንቀለቀለ፣ ደጋፊው እንደተመኘኋት አገኘኋት እያለ እየጨፈረ ነው” … ይህን የተናገረው ከመላው ኢትዮጵያውያን ጆሮ የማይጠፋ ዘመናትን የተሻገረ የሀገር ፍቅርን የሚያስተጋባ ተስረቅራቂ ድምጽ ባለቤት የሆነው ደምሴ ዳምጤ ነው፡፡
ጨዋታን ከመተንተን ባሻገር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ጋር አብረው የሚወሱ አይረሴ ትዝታዎችን አኑሮ ያለፈው ደምሴ ዳምጤ በሚጋባው የሀገር ፍቅር ስሜት ዛሬም በብዙዎች ልብ ውስጥ አለ፡፡
በእግር ኳስ የቀጥታ ሥርጭት ዘገባ (ኮሜንታተርነት) የጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ አይረሴ ትዝታ ከሆኑት ሁነቶች መካከል ኢትዮጵያ ዚምባብዌን በመርታት ሻምፒዮን የሆነችበት የ1980 ዓ.ም የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ሴካፋ ውድድር በዋናነት ይነሳል፡፡
ደምሴ ታሕሳስ 17 ቀን 1980 የተደረገውን የኢትዮጵያ እና ዚምባቡዌ የፍጻሜ ጨዋታ በቀጥታ ሥርጭት ለአድማጮች ያደረሰበት አዘጋገብ ውድድሩ ዛሬም ድረስ እንዲታወስ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ስለመሆኑ በርካቶች ይናገራሉ።
በዚህ ጨዋታ “ዳኙ ገላግለን፣ ወይኔ ወይኔ ገብሬ፣ ውጪ ለቀቃት፣ ዳኙ ደንሶ አገባ” የመሳሰሉት በደስታ ሲቃ የተሞሉት ቃላቶቹ 38 ዓመታት ያስቆጠሩ ቢሆንም የትናንት ያህል ይታወሳሉ፡፡ ይህ ውድድር እሱም በዘመኑ አብዝቶ የሚወደው አጋጣሚ እንደነበር በአንድ ወቅት ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛ ደምሴ በእግር ኳስ የቀጥታ ሥርጭት ዘገባ የጨዋታ እንቅስቃሴዎችን ከመተንተን ባሻገር የደጋፊዎችን ጭንቀት የሚጋራ ደግሞም ደስታን የሚያበስር ለሙያውና ለኢትዮጵያ ስፖርት የተሰጠ ድንቅ ጋዜጠኛ ስለመሆኑ ከመቃብር በላይ የሆኑት ሥራዎቹ ምስክሮች ናቸው፡፡
በድሬዳዋ ገና በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ሳለ በሚኒ ሚዲያ ለተማሪዎች የስፖርት መረጃዎችን በማቅረብ በጀመረው የጋዜጠኝነት መሻት እድሜው 13 ዓመት ሲደርስም ለኢትዮጵያ ሬዲዮ የስፖርት ዜናዎችን ማጠናቀር ጀመረ፡፡
በ1960ዎቹ ለሰባት ዓመታት ያህል በወቅቱ አጠራር ሐረርጌ አውራጃ የሚካሄዱ ስፖርታዊ ክንውኖችን ለኢትዮጵያ ሬዲዮ በመዘገብ በጀማሪ የስፖርት ዘጋቢነት በነጻ አገልግሏል፡፡
በኋላም በ1968 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኢትዮጵያ ሬድዮ በዋናው የሥርጭት ማዕከል በቋሚነት ተቀጥሮ መስራት የጀመረ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ለአራት አስርት ዓመታት ያህል በተጋበት የኢትዮጵያ ሬዲዮ ደማቅ አሻራውን አኑሯል፡፡
በራሱ የአዘጋገብ መንገድ ከመታወቁ አስቀድሞ የወቅቱን ተወዳጅ የስፖርት ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ለመምሰል ስለሚሞክር “ትንሹ ሰለሞን” በመባል ይጠራ ነበር፡፡
አትሌት ደራርቱ ቱሉ በኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊት የሆነችበት የባርሴሎና ኦሊምፒክ ደምሴ ዳምጤ ከሚታወስባቸው ሁነቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
በወቅቱ እምብዛም ለአሸናፊነት ያልተገመተችው ደራርቱ ቱሉ የ10 ሺህ ሜትር ሩጫውን በበላይነት ስታጠናቅቅ ድሉን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማብሰር በውድቅት ሌሊት በእግሩ ወደ ስቱዲዮ የተጓዘበትን አጋጣሚ በኩራት ያስታውሰዋል፡፡
ደራርቱ ውድድሩን አሸንፋ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ስታደርግ በደስታ አነባሁ የሚለው ደምሴ ዳምጤ፥ ከአርሲ ጭላሎ እስከ ባርሴሎና ደማቅ ስኬቷን የሚተርክ ዘገባ ማዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ የደራርቱን አስደናቂ ድል ለሕዝቡ ለማብሰር ሌሊት ወደ ስራ መግባቱን የተረዱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ይህንኑ ጉዳይ ለሕዝቡ እንዲደርስ ካደረጉ በኋላ ከፍተኛ አድናቆትና ክብር እንዳገኘ ገልጿል፡፡
በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ አድሏዊነትና ስሜታዊነትን ማቀብ እንደሚያስፈልግ ጠንቅቄ ባውቅም ብሔራዊ ቡድናችን በሚደርጋቸው ጨዋታዎች ግን ገለልተኛ መሆን አያስችለኝም ሲል ተደምጧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንድ ወቅት በግብጽ አቻው 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ሲሸነፍ ጨዋታውን በቀጥታ ሥርጭት ሲያስተላልፍ የነበረው ደምሴ ዳምጤ ያ አጋጣሚ በሕይወቱ የማይረሳው መጥፎ ገጠመኙ እንደነበር ተናግሯል፡፡
ደምሴ በተለይም በእግር ኳስ የቀጥታ ሥርጭት ተንታኝነት የሕዝቡን ደስታ የሚደሰት ደግሞም ለሕዝቡ ደስታን የሚያጋባ፣ የሀገሩን ጭንቀት የሚጨነቅ፣ በድምጹ የሀገር ፍቅርን የሚያስተጋባ አንደበተ ርቱእ ኮሜንታተር ነበር፡፡
የስፖርት ክንውኖችን አስውቦ ከመዘገብና ጨዋታዎችን በቀጥታ ሥርጭት ከማስተላለፍ ባሻገር በተለይ ለሀገር ውስጥ ስፖርት እድገት ባለው ቀናኢነት ስህተቶች እንዲታረሙ አጥብቆ በመሞገት ይታወቃል፡፡
ደምሴ ዳምጤ በጥቅምት 2005 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት ጊዜ ድረስ በሙያው በተለይም ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ ዛሬም ድረስ እንዲታወስ አድርጎታል፡፡
በተለይም ከ38 ዓመታት በፊት በዚህ ሰሞን የተደረገውና ኢትዮጵያ የዋንጫው ባለቤት የሆነችበት የሴካፋ ውድድር ሲታወስ ጋዜጠኛና ኮሜንታተር ደምሴ ዳምጤን አብሮ ማስታወስ የግድ ይላል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ