የሀገር ውስጥ ዜና

የትራንስፖርት ዘርፍ ችግሮችን ለመፍታት …

By sosina alemayehu

December 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ዘርፍ ችግሮችን ለመቅረፍ ዘመናዊ አሠራርን ማጠናከር ይገባል አለ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመን፣ የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ እና የትራፊክ አደጋን ለመከላከል አሠራርን በማዘመን ጠንካራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ እና የመንገድ ደህንነት ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል።

በሀገሪቱ ያለው የተሽከርካሪ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም የሚደርሰው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የአሽከርካሪዎች የችሎታ ማነስ እና ስነ ምግባር ችግር ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ አብዛኛው የትራፊክ አደጋ በአሽከርካሪዎች ስህተት የሚደርስ መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመፍታትም ትኩረታችንን በአሽከርካሪዎች ብቃት ላይ አድርገናል ነው ያሉት።

ለአብነትም የአሽከርካሪዎችን ስነ ምግባር፣ ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ የስልጠና መስፈርቶችና የብቃት መመዘኛዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

በህገወጥ መንገድ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ፍተሻና የመንጃ ፍቃድ በሚሰጡ ተቋማት ላይ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የትራንሰፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በዚህም በወጪና ገቢ ንግድ፣ በህዝብ ትራንስፖርትና በሰሌዳ አሰጣጥ ላይ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችሉ አሰራሮች ተዘርግተዋል ብለዋል።

በትራንስፖርት ዘርፉ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም እንደ ሀገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተያዘውን እቅድ እውን ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።