የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ሕንድ ያላቸው ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ጠ/ሚ ናሬንድራ ሞዲ

By Melaku Gedif

December 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ሕንድ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸው ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢፌዴሪ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው÷ በአፍሪካ ቅኝ ግዛትን በመገርሰስ ሒደት የአንበሳውን ድርሻ በተወጣችው ኢትዮጵያ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ መልዕክት በማስተላለፌ ክብር ተሰምቶኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና ሕንድ ዲፕሎማሲያዊና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ነው ጠ/ሚ ናሬንድራ ሞዲ ያወሱት፡፡

ኢትዮጵያ እና ሕንድ የሕዝብ ለሕዝብ፣ የታሪክ እንዲሁም የባሕል ትስስር ያላቸው ሀገራት እንደሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያና ሕንድ ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው÷ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሳይበር ደህንነት፣ አቅም ግንባታ፣ ግብርና፣ ትምህርት እና ጤና ዘርፎች ላይ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታ ዘርፍ የሀገራቱ ትብብር አስፈላጊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዘርፉ በቅንጅት የመሥራቱ ሒደት እንደሚጠናከር አመላክተዋል።

ጠ/ሚ ናሬንድራ ሞዲ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለተደረገላቸው የክብር አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል፡፡