አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ህንድ ትብብር ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን የሚፈታ እና አዳዲስ እድሎችን የሚፈጥር እንዲሆን በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የክብር እራት ግብዣ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በወቅቱ እንዳሉት፤ በዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ ስልጣኔዎች መካከል በሆነችው ሀገር መከበር ታላቅ ኩራት ነው።
ኢትዮጵያ ለሁላችንም ትልቅ የመነሳሳት ምንጭ የሆነች ሀገር ናት ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አመራር የሚያከናውነው ተግባር የሚደነቅ እንደሆነ አንስተው፤ በተለይም የመደመር ራዕይ እና የልማት ቁርጠኝነት ኢትዮጵያን በብልጽግና ጎዳና ላይ ለማራመድ እየተጓዘ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በአካታች ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በዲጂታል ሽግግር፣ በኢኮኖሚ እድገት እና ሌሎች ዘርፎች የምታከናውነው ተግባር ምሳሌ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
የህንድ እና የኢትዮጵያን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለ ገልጸው፤ የሁለቱ ሀገራት ትብብር ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን የሚፈታ እና አዳዲስ እድሎችን የሚፈጥር እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የተበረከተላቸው ከፍተኛ የክብር ኒሻን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጠንካራ እንዲሆን አስተዋጽኦ ባደረጉ ህንዳውያን ስም የተቀበሉት እንደሆነም ገልጸዋል።
በዮናስ ጌትነት