የሀገር ውስጥ ዜና

ለአካል ጉዳተኞች ያለውን የሥራ እድል ተሳትፎ ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ

By Melaku Gedif

December 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለወጣት አካል ጉዳተኞች ያለውን የሥራ እድል ተሳትፎ ለማጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ላይት ፎር ዘዎርልድ የተሰኘው ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅትም ለወጣት አካል ጉዳተኞች የሥራ እድል ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡

በላይት ፎር ዘዎርልድ የኢንክሉሲቭ ኢምፕሎይመንት ኦፊሰር ተስፋነሽ ጣለው እንደሚሉት÷ በተለያዩ ዘርፎች ተመርቀው ሥራ ያላገኙ አካል ጉዳተኛ ወጣቶችን የክህሎት ሥልጠና በመስጠት የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም የመንግሥትና የግል ተቋማት ክፍት የሥራ ቦታ ሲኖር አካል ጉዳተኛ ወጣቶችን እንዲያሳትፉ የሚያስችል ውይይት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ተቋማቱ ፈቃደኛ ከሆኑም አካል ጉዳተኞች በመስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን የሥራ ልምምድ በማድረግ ብቁ ሲሆኑ መደበኛ ሥራ እንደሚጀምሩ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ሒደትም አካል ጉዳተኛ ወጣቶች በተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት የሥራ እድል እንዲያገኙ መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡

ይህን ተከትሎም ለአካል ጉዳተኛ ወጣቶች ቋሚ የሥራ እድል ላመቻቹ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት የእውቅና መስጠት መርሐ ግብር መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

ለአካል ጉዳተኛ ወጣቶች ያለውን የሥራ እድል ተሳትፎ ለማጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡