አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዋሽ ካፒታል አክሲዮን ማህበር በአዲሱ የካፒታል ገበያ ማዕቀፍ በይፋ ሥራ ጀምሯል።
የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ እና የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀሐይ ሽፈራው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ ምዕራፍ በመግባት ዘርፈ ብዙ ለውጦችን እያደረገች ትገኛለች።
ከለውጡ መካከል የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን መቋቋም መሆኑን ገልጸው፤ የተቋሙ ወደ ስራ መግባት ለፋይናንስ ዘርፉ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ ነው ብለዋል።
አዋሽ ካፒታል አክሲዮን ማህበር አስፈላጊውን መስፈርት እና መመዘኛ አሟልቶ ሙሉ የኢንቨስትመንት ባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን መቀበሉን ተናግረዋል።
የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አንዱአለም ኃይሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አክሲዮን ማህበሩ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ባንክ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በድርጅት ፋይናንስና የማማከር አገልግሎት፣ በዋስትና ንግድና የማገናኘት ስራ፣ በምርምርና የገበያ ኢንተለጀንስ፣ በአረንጓዴ ፋይናንስ እንዲሁም የከባባዊ፣ ማህበራዊና አስተዳዳራዊ (ኢኤስጂ) የማማከር አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
አክሲዮን ማህበሩ በ200 ሚሊየን ካፒታል ስራ የጀመረ ሲሆን፤ ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በተገቢው ሁኔታ ራሱን በማደራጀት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ተመላክቷል።
በዮናስ ጌትነት