ቢዝነስ

በኦሮሚያ ክልል የአምራች ነጋዴ የገበያ ትስስርን ለማሳለጥ …

By Melaku Gedif

December 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ በክልሉ በአምራቾች እና በነጋዴዎች መካከል ያለውን የገበያ ትስስር ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አንዷለም አበበ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ዘላቂ የዋጋ መረጋጋትን ለመፍጠር የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በዚህም መሰረት አምራቾች ምርታቸውን በተገቢ ሁኔታ ለነጋዴዎች እንዲያስረክቡ አስፈላጊውን የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለገበያ እንዲቀርቡና ለሸማቹ ማሕበረሰብ ተደራሽ እንዲሆኑ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን የማስፋት ሥራ መሰራቱን አመልክተዋል፡፡

አሁን ላይ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ660 በላይ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ በቀጣይ በማዕከላቱ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት፣ መጠንና ዓይነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ለምርቶች ዋጋ መጨመር መንስኤ የሆኑት ሕገ ወጥ ደላላዎች እና ኬላዎች ላይ ርምጃ በመውሰድ ከገበያ ሥርዓት የማስወጣት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ምርት በመደበቅ አላስፈላጊ የገበያ አለመረጋጋት ለመፍጠር የሚሰሩ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ርምጃ እየተወሰደ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

ሕብረተሰቡ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ እና ምርቶችን የሚያከማቹ ነጋዴዎችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በቴክኖሎጂ የታገዘ ኢትሬድ ሥርዓት በመዘርጋት ነጋዴዎች ባሉበት ሆነው በኦንላይን አገልግሎ እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራት ለ74 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ንግድ ፈቃድ በኦላይን የተሰጠ ሲሆን÷ 73 በመቶ የሚሆኑ ነጋዴዎች ደግሞ ንግድ ፈቃዳቸውን በኦንላይን አድሰዋል፡፡

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በዓይነትና መጠን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ