አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ እና ህንድ ግንኙነት በስትራቴጂክ አጋርነት አዲስ ከፍታ ላይ ደርሷል አሉ፡፡
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በዚህ ሳምንት የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጠናከር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ያደረጉትን የኢትዮጵያ ጉብኝት አስመልክቶ ከዲዲኢንዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናከረ ነው ብለዋል።
ይህም ሀገራቱ ያላቸውን የልማት ትብብር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ወደ ላቀ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ከፍ አድርጓል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ እና ህንድ ግንኙነት ከዲፕሎማሲ ባለፈ በታሪክ እና በባህላዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጉብኝት ግንኙነቱን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ጉብኝቱ ለጋራ ልማት ጅምሮች አዳዲስ ዕድሎችን ይከፍታል ያሉት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ ትብብሩ በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና እና በቴክኖሎጂ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ህንድ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በግብርና ቴክኖሎጂ ያላት እውቀት ጠቃሚ የመማር እድሎችን እንደሚሰጥም አብራርተዋል።
ህንድ ለጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል በተለይም ለእናቶች ጤና ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸው፤ ይህም የእናቶች እና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ፍሬያማ እንደነበር ገልጸው ይህ ጉብኝት መጨረሻ ሳይሆን የታደሰ እና የተጠናከረ አጋርነት መጀመሪያ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!