ቢዝነስ

በኦሮሚያ ክልል በተኪ ምርት ከ850 ሚሊየን ዶላር በላይ ማስቀረት ተቻለ

By Yonas Getnet

December 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት በተኪ ምርት 856 ሚሊየን ዶላር ማስቀረት ተችሏል አለ።

በቢሮው የማኑፋክቸሪንግ ክትትል፣ ድጋፍ እና ቁጥጥር ዳይሬክተር ቦንቱ ተሾመ (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ልዩ ጥረት እየተደረገ ነው።

ከዚህ ቀደም በውጭ ይገቡ የነበሩ 93 ዓይነት ምርቶችን በመለየት በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ከ161 በላይ ፋብሪካዎች ተኪ ምርቶችን እያመረቱ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ፋብሪካዎቹ የግንባታ፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ የምግብ ሸቀጦችን ጨምሮ በርካታ ከውጭ ሀገራት ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በስፋት እያመረቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

እንዲሁም ዘርፉን ለማጠናከር መንግሥት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ልዩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ለወጪ ንግድ እና ለተኪ ምርቶች እኩል ትኩረት ተሰጥቷል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርት እየተመረተ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ እየቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።

በሲፈን መገርሳ