አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በዘመን ገበያ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አዲስ አሰራር ይፋ አድርጓል።
አገልግሎቱ የኢንዱስትሪ ምርቶች በዘመን ገበያ የዲጂታል ግብይት ስርዓት አማካኝነት ለተጠቃሚዎች የሚቀርቡበት ነው።
ሁለቱ ተቋማት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ አምራቾችን ወደ ዘመን ገበያ በማስገባት ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገር ውስጥ ሸማቾች እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ፈርመዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በወቅቱ እንዳሉት፥ በዲጂታል የግብይት ስርዓት የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን ለመፍታት በስፋት መስራት ይገባል።
በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ይፋ ያደረገውን የግብይት ስርዓት ውጤታማ ለማድረግ የሚመለከታቸው ተቋማት ትብብርን አድንቀዋል።
ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዛሬ ይፋ የተደረገው አሰራር በተለይም በዲጂታል ግብይት ዘርፍ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
በሀገራችን በተበታተነ ሁኔታ በጅምር ላይ የሚገኘውን ኤሌክትሮኒክ የግብይት ስርዓት በመደበኛነት ለማስቀጠል ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
በአምራች ዘርፉ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ከመላክ ባሻገር በዘመናዊ የንግድ ስርዓት ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ዲጂታል የግብይት አገልግሎቱ አምራቾች ሰፊ የሀገር ውስጥ የገበያ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ በግብይት ሂደት የሚያወጡትን ወጪ ለመቀነስ ያስችላል።
በዲጂታል ግብይት ስርዓቱ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ምርቶች፣ ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም የህክምና የግንባታ ግብዓቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ይቀርባሉ።
በኃይለማርያም ተገኝ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!