ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ሶሪያ በሚገኘው የአይኤስ ቡድን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ፈጸመች

By Melaku Gedif

December 20, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ጦር በሶሪያ በሚንቀሳቀሰው የአይኤስ ሽብር ቡድን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ፈጽሟል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት ÷ ጥቃቱ የአይኤስ ሽብር ቡድን በቅርቡ ሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ለፈጸመው ጥቃት የተወሰደ አጸፋዊ ርምጃ ነው፡፡

በተፈጸመው መጠነ ሰፊ ጥቃትም ከ70 በላይ በሚሆኑ የአይኤስ ይዞታዎች ላይ ኢላማ መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡

ለጥቃቱ የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ ተዋጊ ጄቶች፣ ሔሊኮፕተሮች ፣ መድፎች እና ሌሎች ጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ሬውተርሰ ዘግቧል፡፡

ተዋጊ ጄቶችና ሔሊኮፕተሮች ከዮርዳኖስ በመነሳት በአይኤስ ይዞታዎች ላይ የፈጸሙት የአየር ላይ ጥቃት ስኬታማ እንደነበር ፕሬዚዳንት ትራምፕ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአይኤስ የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘኖች፣ የቡድኑ ታጣቂዎች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስ መቻሉን አመልክተዋል፡፡