አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአፈር ለምነትንን በማሻሻልና ውሃን በማቀብ በአነስተኛ ወጪ ከፍተኛ ምርት ማስገኘት የሚያስችለውን የእቀባ እርሻ ዘዴ በመጠቀም ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አድማሱ አወቀ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፥ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች የተፈጥሮ ክስተቶች የሚያስከትሉትን ተጋላጭነትን ለመቋቋም የእቀባ እርሻ ዘዴ በክልሉ በስፋት እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ግብርናን ከመፍጠር አንጻር ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዘማች ሶርሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው በተለይ ለዝናብ እጥረት በሚጋለጡና ተደጋጋሚ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል በመሆኑ ይበልጥ ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጠረጴዛ ልማት ማህበር በክልሉ የእቀባ እርሻ ዘዴን ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅና የማላመድ ስራ ከሚያከናውኑ ማህበራት አንዱ ሲሆን፥ በ11 ወረዳዎች ከ80 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተደራሽ ማድረጉን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ በረከት ጣሰው ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ ሽፋን ሰብሎችና ተረፈ ምርቶችን በጉዝጓዝነት በመጠቀም የአፈር መሸርሸርን በመቆጣጠር፣ የአፈር ርጥበትን በመጨመርና የመሬት መራቆትን በማስቀረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡ በልማት ማህበሩ ባገኙት ድጋፍ የእቀባ እርሻ ዘዴን ተግባራዊ ያደረጉ አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም በልማዳዊ የግብርና ዘዴ ከሚያገኙት የተሻለ ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በመለሰ ታደለ