አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወደ ስራ እየገቡ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች በዓይነትም ሆነ በመጠን የተለዩ ስትራቴጂክ ምርቶችን የሚያመርቱ ናቸው አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ የተመራ ቡድን በደብረብርሃን ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ አምራች ኢዱስትሪዎች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ መመልከትና እያጋጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶችን በቅንጅት ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄ ለመስጠት እንደሆነ ተገልጿል።
አቶ መላኩ አለበል በወቅቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪዎቹ በምን ቁመና ላይ ይገኛሉ የሚለውን ማየት ተችሏል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ያሉባቸውን ማነቆዎች መለየትና የፖሊሲ መፍትሄ መስጠት የብሔራዊ ካውንስሉ ዋና ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በአማራ ክልል ከወትሮው በተሻለ መልኩ አዳዲስና ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ገብተዋል ነው ያሉት።
ብሔራዊ ካውንስሉ በጉብኝቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከኃይል አቅርቦት፣ ከግብዓት እጥረት እና ከፋይናንስ ጋር የተገናኙ ችግሮች እንዳሉ መመልከቱን ገልጸው፤ ችግሮቹን ለመፍታትም የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በዓለምሰገድ አሳዬ