ጤና

የኢትዮጵያን ባሕላዊ ምግቦች ይበልጥ ለማስተዋወቅ…

By Melaku Gedif

December 21, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ከሕዝቦች ባሕልና እና ማንነት የተቀዱ በርካታ ባሕላዊ ምግቦች ይገኛሉ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ተስፋዬ ባንጎ እንደሚሉት ÷ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከባህላዊ የምግብ አሰራር ጀምሮ በርካታ አይነት ሀገር በቀል እውቀቶች አሉ፡፡

ይሁን እንጂ ባሕላዊ ምግቦችን በሀገር ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ተፈላጊነታቸውን ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ ውስንነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

ሀገር በቀል ምግቦች ይዘታቸውና ጥራታቸውን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ባህላዊ ምግቦች ከፍተኛ ንጥረ ነገር እንዳላቸው የገለጹት አቶ ተስፋዬ÷ ይህም የተመጣጠነ ምግብ በመስጠት ለእዕምሮ እድገትና ለአካላዊ ጥንካሬ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አብራርተዋል፡፡

በተለይም በአርሶ አደሩ ማሳ የሚገኙ ሀገር በቀል ምግቦች ያላቸውን የጤና ጠቀሜታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በከተማ ሆቴሎች ውስጥ በስፋት ማቅረብ እንደሚገባ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዘላቂ ሥርዓተ ምግብና ግብርና ህብረት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ባዩሽ ጸጋዬ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ሁለንተናዊ ተደራሽነት ለማስፋት የማስተዋወቅ ሥራን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡፡

አሁን ላይ ቀድሞ የነበሩን የሰብል ዝርያዎችና ባህላዊ ምግቦች እየተመናመኑ መምጣታቸውን ጠቁመው÷በተለይም በከተሞች አካባቢ የታሸጉ ምግቦች እየተዘወተሩ ነው ብለዋል፡፡

ስለሆም የራሳችንን ባህላዊ ምግብ ተገቢ በመሆነ መልኩ በማሳደግና አሰራሩን በማዘመን ማስፋትና መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

ከዚህ ባለፈም የባሕላዊ ምግብ አሰራሮችን በትምህርት ፖሊሲ እንዲካተቱና ወጣቱ ትውልድ በሚገባ ተረድቶ እንዲያጠናክር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ለማስተዋወቅና ለጤና ያላቸውን ጠቀሜታ ለሕብረሰተቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተካሄደው መድረክ አላማም ይሄው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ዘላቂ ግብርናን አጠናክሮ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት እንዲገባ አመልክተዋል፡፡