አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወጣቶች በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በቅርስ ጥበቃና መከላከል ሥራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በሔሪቴጅ ዎች የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሄለን ዘርአይ እንደሚሉት÷ የአንድ ሀገር ቀጣይ ሕልውና የሚረጋገጠው ወጣቱ ትውልድ ለተፈጥሮ ያለውን መረዳት በማሳደግ አካባቢን ሲጠብቅና ሲንከባከብ ነው፡፡
ለዚህም ወጣቱ ሀገሩን ተንከባክቦ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲችል ሔሪቴጅ ዎች ኢትዮጵያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ወጣቱ ትውልድ ላይ ስለአየር ንብረት ለውጥ፣ አካባቢ ጥበቃ እና ቅርስ እንክብካቤ አስፈላጊውን ግንዛቤ ለመመፍጠር በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቶች በኢትዮጵያ የሚዳሰሱና የማይዳሱ ቅርሶችን ከመጠበቅ ባለፈ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ የማሳተፍ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥና አካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞም ከት/ቤቶ ጋር ትስስር በመፍጠር ተማሪዎች በት/ቤቶች ቅጥር ግቢ ሀገር በቀል እጽዋትን በመትከል የበኩላቸውን እንዲወጡ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በቅዱስ ዩሴፍ፣ንጋት ኮከብ፣ ጀርመን ኤምባሲና ቀበና አድቬንቲስት ት/ቤቶች ውስጥ በትብብር የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ማጠቃለያ መርሐ ግብር መካሄዱን የተናገሩት ደግሞ የፕሮጀክቱ ማኔጀር ቤተልሄም ገ/መድህን ናቸው፡፡
በት/ቤቶቹ ጋርደን የተከናወኑት የአየር ንብረት ለውጥ፣ አካባቢ ጥበቃ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በሥራው ሒደት መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ የትምህርት ማሕበረሰቡ እንዲሁም ነዋሪዎችን ማሳተፍ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
በዘርፎቹ ወጣቶች ጋር መስራት አስፈላጊ ነው ያሉት ፕሮጀክት ማናጀሯ ÷ የወጣቶችን አስተሳሰብ መቅረጽ ለዘላቂ አየር
ንብረት ለውጥ ፣አካባቢ ጥበቃና ቅርስ እንክብካቤ ሥራ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ወጣቶች በመሰል ሥራዎች ላይ ተሳትፏቸው እንዲጠናከርና ያላቸውን ሚና እንዲያድግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡