የሀገር ውስጥ ዜና

ከጊዜ ወደ ጊዜ የፌዴራል ተቋማት ኢትዮጵያን እየመሰሉ የመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል – አቶ አደም ፋራህ

By Abiy Getahun

December 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ አካታችና አሳታፊ ስራዎች የፌዴራል ተቋማት ኢትዮጵያን እየመሰሉ የመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል አሉ፡፡

አቶ አደም ፋራህ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ ብልጽግና ፓርቲ እንደ መሪ ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአባልነት እና በአመራርነት ያቀፈ ነው።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ከተሰጣቸው 76 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል ሁሉም በአመራርነት ያሉበት ፓርቲ ነው ብለዋል።

ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር ውስጥ የሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮችን እናገኛለን በማለት ገልጸዋል።

የፌዴራል ተቋማት ኢትዮጵያን እንዲመስሉ ሁሉም በውስጣቸው በመሳተፍ ሲቪል ሰርቫንት እና አመራር ሆነው ለማገልገልም የሚያስችል ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች የፌዴራል ተቋማት ኢትዮጵያን እየመሰሉ የመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚ አካታችነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በፌዴራል ደረጃ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶችን ፍትሃዊ እና ተመጣጣኝ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ በጥናት በመለየት ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።

ስምንት የፌዴራል መሰረተ ልማት ተቋማት ተመርጠው ከዚህ ቀደም ሲመሯቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ሂደት መፈተሹን አስረድተዋል።

የፕሮጀክቶች ዕቅድ፣ ቅደም ተከተል፣ ፍትሃዊነት እንዲሁም ጥንካሬና ድክመታቸው ተለይቶ ግልጽ የሆነ መስፈርት እና የአሰራር ስርዓት ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር የሚገባበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በዚህም ከዚህ ቀደም ከፍትሃዊነት አኳያ የነበሩትን ጉድለቶች በሚሞላ መልኩ አፈጻጸሙ መሻሻል አምጥቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ክልሎች በፌዴራል መሰረተ ልማት ተቋማት የሚሰሩ ስራዎች ፍትሃዊ መሆናቸውን እየመሰከሩ መሆኑን ገልጸው፤ ተመጣጣኝ ዕድገት ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል ነው ያሉት።

በቀጣይም የአፈጻጸም ልዩነቶችን በማጥበብ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል።

በአቢይ ጌታሁን