ቴክ

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካታች የቴክኖሎጂ እድገትና ፈጠራን ለማፋጠን…

By Mikias Ayele

December 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካታች የቴክኖሎጂ እድገትና ፈጠራን ያግዛል አሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉቀን ቀሬ፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ገለጻ፥ እቅዱ የምናልማት ኢትዮጵያ ፈጠራዎቿ በሀገራዊ ማንነት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ከዲጂታል 2030 ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል በስራ ፈጠራ፣ በተሸጋገሩ ስታርታፖች፣ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንትርፕራይዞች እንዲሁም በዘመኑ ቁልፍ ሴክተሮች አካታች የዲጂታል ስርዓትን ማፋጠን አንዱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨሰትመንት የዲጂታል ዘርፉ አንቀሳቃሽ ሞተር እንዲሆን ለማድረግ ያለመ ዕቅድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ የሚያስችል የዲጂታል ክህሎት ልማትና የቴክኖሎጂ ስነ ምህዳር ለመፍጠር ዲጂታል 2030 ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት በዲጂታል ክህሎት የሰለጠነ እንዲሆን ማድረግ የእቅዱ አካል መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ብሔራዊ ዲጂታል ስታራቴጂን እውን ማድረግ፣ አምራች የሰው ኃይል ማፍራትና የቴክኖሎጂ ትምህርት ስርዓት ለውጥ የእቅዱ መሰረታዊ ምሶሶዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ