ቢዝነስ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ27 ቢሊየን ብር በላይ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

By sosina alemayehu

December 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ27 ቢሊየን ብር በላይ የብድር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንዳሉት፤ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ቦታ ያለው እንዲሆን በማድረግ ረገድ የድርጅቱ ሰራተኞች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

አየር መንገዱ ከዚህ በፊት ለሰራተኞቹ 1 ሺህ 200 ቤቶችን ገንብቶ ማስረከቡን አስታውሰው፤ አሁን ላይ 5 ሺህ ቤቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ይህ የቤት ግንባታ እንዲሳካ ለማድረግ በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ27 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የብድር ስምምነት መፈረሙን ነው የገለጹት።

የብድር ስምምነቱ ለረዥም ዓመታት የዘለቀውን የሁለቱን ተቋማት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሰው እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፤ ባንኩ የብድር አገልግሎትን በበቂ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በተለይም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የብድር አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ምህዳር ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

በዛሬው ዕለት ከአየር መንገዱ ጋር የተፈረመው ስምምነት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝ ጠቁመው፤ ተቋማቱ በሀገራዊ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት