የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የትብብር ስምምነት ፈረሙ

By Abiy Getahun

December 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የጤና ትብብር ማዕቀፍ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የትብብር ማዕቀፉ ውስጥ የአሜሪካ መንግስት 1 ነጥብ 16 ቢሊየን ዶላር የሚያቀርብ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር ውስጥ የጤና ስርዓትን ፋይናንስ ለማሳደግ በያዘው ዘላቂ መሰረት ቀሪውን ፋይናንስ የሚሸፍን ይሆናል።

ትብብሩ ለአምስት ዓመት ለጤና ዘርፍ ዘላቂ ልማት እና የጋራ ኢንቨስትመንት ማጠናከሪያ ትብብር የሚውል ነው።

የመግባቢያ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ፈርመዋል።

ድጋፉ በኢትዮጵያና አሜሪካ ትብብር ታሪካዊ የተባለለት ሲሆን የአዲሱ የትብብር ምዕራፍ የጠበቀ ግንኙነት ማሳያ እንደሆነም ተነስቷል።

120 ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ወዳጅነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ሲገለጥ መቆየቱ ይታወሳል።

በአሸናፊ ሽብሩ