አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ10 ወራት በኋላ የኮባልት ማዕድንን ዳግም ወደ ውጪ ሀገራት መላክ ጀመረች፡፡
ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮባልት አቅርቦት መጨመሩን ተከትሎ የማዕድኑ ዋጋ በመቀነሱ ወደ ውጪ መላክ አቋርጣ ቆይታለች፡፡
ማዕድኑ የስማርት ስልኮችና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ባትሪ ለማምረት እንደሚውል የተገለጸ ሲሆን፥ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ በዓለም ቀዳሚዋ የኮባልት አምራች ሀገር ናት፡፡
የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ዱዱ ፍዋምባ እንዳሉት፥ ሀገሪቱ ለአስር ወራት ያህል አቋርጣው የነበረውን የኮባልት ማዕድን ኤክስፖርት ባለፈው አርብ ዳግም ጀምራለች፡፡
ሀገሪቱ በዓለም ከ70 በመቶ በላይ የኮባልት ማዕድንን እንደምታቀርብ የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ነገር ግን ዋጋውን መወሰን አለመቻሏ ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት፡፡
ምርቱን ለዓለምአቀፍ ገበያ ማቅረብ ያቆመችውም በዚሁ ምክንያት መሆኑን ሚኒስትሩን ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በፈረንጆቹ 2024 ከዓለም የኮባልት ማዕድን ምርት 76 በመቶ ያህሉን ማቅረቧን የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ ያመለክታል፡፡
በአቤል ነዋይ