የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 456 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን..

By Melaku Gedif

December 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ከ456 ሺህ በላይ ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ ፡፡

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት እንዳሉት÷ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተራቆቱ አካባቢዎችን በማልማት ለግብርና ሥራ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት ለሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በአማራ ክልል ከ456 ሺህ በላይ ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን እቅድ መያዙን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ዜጎች በአፈርና ጥበቃ ሥራ ንቅናቄው በንቃት እንዲሳተፉ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መከናወኑን ለፋና ዲጂታል አብራርተዋል፡፡

በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሚሳተፉ ሲሆን ÷ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የቁፋሮ እና ሌሎች መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የሚከናወንባቸው 9 ሺህ 200 በላይ ተፋሰሶች መለየታቸውን ነው የገለጹት፡፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለአፈር ለምነት ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ማሕበረሰቡ በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ