የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ የአየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከጥር 15 እስከ 19 ይከበራል

By sosina alemayehu

December 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የአየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከጥር 15 እስከ 19/2018 ዓ.ም በተለያዩ መርሐ ግብሮች ይከበራል።

በኢትዮጵያ አየር ኃይል የ1ኛ አየር ምድብ አዛዥና የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ብ/ጄነራል ብሩክ ሰይፉ በሰጡት መግለጫ፥ በዓሉ “የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡

“የአንበሶች ሰማይ! ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ ሀገራት አየር ኃይሎች በጋራ በመሆን የጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ይካሄዳል ብለዋል።

የበዓሉ አካል የሆነ የ10 ኪሎ ሜትር ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር “ለአየር ኃይል እድገት በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ባሳለፍነው ሕዳር 21 በቢሾፍቱ ከተማ መካሄዱን አስታውሰዋል።

“የወደፊቱን የአቪዬሽን አቅም በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ ከ25 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2026 እንደሚካሄድም ነው ያስረዱት፡፡

በኤክስፖው ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም የቻይና፣ የህንድ፣ የአሜሪካና የደቡብ አፍሪካ ትላልቅ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከ38 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች የሚሳተፉበት ፊውቸር አፍሪካ የአየር ኃይሎች ፎረም “የጋራ ስራዎቻችንን አጠናክረን የተረጋጋ ዓለም እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ ለ3ኛ ጊዜ ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡

“ሀገርን በማገልገል የሚገኝን ክብር መዘከር” በሚል መሪ ሀሳብ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ህዝባዊ ውይይት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን መርሐ ግብሮች በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፥ ህብረተሰቡ በምስረታ በዓሉ ላይ በመገኘት ያገለገሉትንና እያገለገሉ ያሉ የአየር ኃይል አባላትን እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም አየር ኃይሉ ያዘጋጀውን ድህረገጽ etaf90years.com በመጠቀም በበዓሉ የሚካሄዱ ሁነቶችን መከታተልና የመግቢያ ቲኬት መግዛት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በዮናስ ጌትነት