አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ተጨማሪ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማለም እድል የፈጠረ ነው አሉ።
“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ ስለ ኢትዮጵያ የውይይት መድረክ በጉባ ተካሂዷል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ ወቅት ÷ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ተጨማሪ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማለም እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ያላትን ሃብት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ በተግባር ያሳየና መሰረታዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሕዳሴ ግድብ ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠር እና ወንድማማችነትን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በየዓመቱ እያደገ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም መንግሥት በኃይልና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያደረገው የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል ነው ያሉት።
ይህም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ያሉት ፍስሃ (ዶ/ር)÷ በተለይ በኃይል ዘርፍ የተከናወነው የመሠረተ ልማት ግንባታ ለኢንዱሰትሪው እድገት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ባለፉት 20 ዓመታት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ኃይል ዝቅተኛ መሆኑን ገልፀው÷ አምና በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሶላር ምርቶችን የሚያመርት ፋብሪካ ሥራ በመጀመሩ ከፍተኛ ሐይል ጥቅም ላይ መዋሉን ገልፀዋል።
በቀጣይ ዓመታት ግዙፍ ፋብሪካዎች የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚቀላቀሉ በመሆኑ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች 2 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ብልጽግና በተግባር የሚያሳይ ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴዔታ መሠረት ኃይሌ ናቸው፡፡
ሕዳሴ ግድብ የሕዝቦች አብሮነት የተንጸባረቀበትና ለትውልድ የሚተላለፍ የታሪክ አሻራ መሆኑን ገልጸው÷ በተለይም ለኢንዱስትሪ ምርታማነትና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በተለይም ዲጂታላይዜሽንን እውን በማድረግ በሁሉም ዘርፎች ስኬታማ ስራዎች እንዲሰሩ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ የይቻላል መንፈስን የፈጠረ ነው።
በግድቡ ግንባታ የታየውን ሕብረት በሌሎች ሥራዎች ላይ እውን ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።