አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ በክልሉ ከ3 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው አለ።
የቢሮው ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መስፍን ተስፋዬ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ቢሮው በአራት ዋና ዋና ግቦች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡
የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ቀጣይነትን ማረጋገጥ፣ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂን በማስፋፋት የማህበረሰቡን ህይወት ማዘመን እንዲሁም የስራ ዕድል መፍጠር ዋና ዋና ግቦች እንደሆኑ አብራርተዋል።
የክልሉ መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመጠጥ ውሃ አገልግሎትን የማስፋፋት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከመንግስት በጀት፣ ከህዝብ ተሳትፎ እና ከተለያዩ መርሐ ግብሮች በአጠቃላይ 3 ሺህ 274 የውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሆኑ አስታውሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማስፋፋት ከ62 ቢሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ 2 ሺህ 266 ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ከ3 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ገልጸው፤ እስካሁን 364 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል ነው ያሉት።
ቀሪ ፕሮጀክቶች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በፀሐይ ጉልማ