አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሰባሳቢ ትርክትን በውስጡ የያዘው ‘ዳራሮ’ የዓለም ቅርስ እንዲሆን ማስተዋወቅ ይገባል አሉ የጌዴኦ ባህላዊ የባሌ አስተዳደር ሥርዓት መሪ አባገዳ ቢፎም ዋቆ።
የዳራሮ ባህላዊ እሴቶች አብሮነትና የልማት ተሳትፎን የሚያጠናክሩ አሰባሳቢ ትርክትን የያዙ በመሆኑ ትውልዱ አጥብቆ ሊይዛቸው እንደሚገባም አባገዳ ቢፎም ዋቆ ይመክራሉ፡፡
አባገዳ ቢፎም እንደሚሉት፥ በሰባቱ የጌዴኦ ብሔረሰብ ጎሳዎች ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት ሠላማዊ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል የመንፃት ባህል አለ፤ ይህ ባህል ‘ፋጭኤ’ በመባል ይታወቃል፡፡
በቤተሰብ ደረጃ የሚፈጠር ቁርሾ አድጎ ለሀገርም ይተርፋል የሚሉት አባገዳው፥ ዳራሮ ይህ ከመድረሱ በፊት በፋጭኤ ስርዓት በይቅርታና እርቅ ችግርን የመፍታት ልማድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህም በሕዝቦች መካከል ሰላም እንዲኖርና በቂ ዝናብ፣ ፀሐይ እና ንፁህ አየር ከፈጣሪ ዘንድ ወቅቱን ጠብቆ እንዲመጣ መፀለይን ያካትታል ነው ያሉት።
ሥነ ስርዓቱ በአባ ገዳ መናገሻ ‘ኦዳ ያአ’ ስፍራ ተጀምሮ በየደረጃው በተለያዩ አካባቢዎች ከተከናወነ በኋላ ማጠቃለያውን በዳራሮ በዓል ያደርጋል፡፡
ዳራሮ በውስጡ አንድነትን፣ እርስ በርስ መደጋገፍን እንዲሁም ቁርሾ በእርቅ የሚወገድበት ፋጭኤ (መንጻት)፣ ምስጋና፣ ይቅርታ፣ ምርቃት፣ ልገሳና መከባበርን የያዘ የአሰባሳቢ ትርክት ምልክት ነው ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርቤ ጂኖ በበኩላቸው፥ እንደ ሀገር ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ቱባ ባህሎችን ለዓለም የማስተዋወቅ እድል መፍጠሩን አነስተዋል፡፡
በትውልድ ቅብብሎሽ በእንክብካቤ የቆየው ጥብቅ ደንና መልክዓ ምድር በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በጌዴኦ ዞን ለህብረተሰቡ አንድነትና ለዘላቂ ሰላም መሰረት የሆኑ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁ፣ እንዲለሙና እንዲተዋወቁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ የዳራሮ ባህላዊ እሴቶች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስር በማሳደግ የልማት ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እያገዘ ሲሆን፥ እሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የሁሉም አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመለሰ ታደለ