አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላ 5 ልጆችን ለስራ ስምሪት ወደ አውሮፓ ሀገራት እልካችኋለሁ በማለት ገንዘብ ሲቀበል የነበረ ግለሰብ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እና በገንዘብ ተቀጣ።
የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ነው።
ግለሰቡ ንጋት አጠኔ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና በሰዉ የመነገድ እና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 8 (3) ስር የተመላከተዉን በመተላለፍ ክስ ቀርቦበታል።
በዚህም ተከሳሽ ካልተያዙ ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የግል ተበዳይ የሆነዉን ሕጻን አብዱልሳላም ሸሊላ ከኢትዮጵያ ወደ ሊቢያ ከዛም ወደ አውሮፓ እንደሚልከዉ ከማህበራዊ ሚዲያ መካከል አንዱ በሆነው በኢሞ በማውራት የማሳመን ስራ ሰርቷል፡፡
ከምራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ኤዶ ከተማ ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ከግል ተበዳይ አብዱልሰላም ሙሃባ እና ፈልማታ መሃመድ ከተባለዉ ጋር ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ አዲስ አበባ ደርሰዉ ከኢሞ ባገኙት ስልክ ለተከሳሽ ደውለው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አዉቶቡስ ተራ ተገናኝተዉ ለመታወቂያ የሚሆን ፎቶ ግራፍ በስልክ አንስቶ ይዞ በመሄድ የአዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂያ ማዘጋጃ የሚሆን ከእያንዳንዳቸዉ 500 ብር ተቀብሏል፡፡
በሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር የሚሄዱበትን የአውሮፕላን ጉዞ ቲኬት እና ጎንደር ሲደርሱ የሚቀበላቸው ዳንኤል የሚባል የአባቱ ስም በትክክል የማይታወቅን ግለሰብ ስልክ ቁጥር በመስጠት እንዲሄዱ አድርጎ በተሰጠጣቸው ስልክ ቁጥር ደውለው ዳንኤል የተባለዉን ካገኙ በኋላ ከሌሎች ግብረ አበሮች ጋር በመሆን የግል ተበዳዮች የያዟቸውን የስልክ ቀፎዎች እና አዲስ አበባ የተሰጣቸዉን የነዋሪነት መታወቂያ በመቀበል እያንዳንዳቸው ብር 1 ሚሊየን 600 ሺህ ብር እንዲከፍሉ በመንገር ንጉስ ወደተባለ ሆቴል ወስደው አንድ ክፍል ውስጥ 6 ሆነዉ ለሶስት ቀናት እንዲኖሩ አድርገዋል።
አብዱልሰላም ሸሊላ የተባለውን የግል ተበዳይ ስም አለሙ አየለ ሃይማኖት ኦርቶዶክስ በሚል በመቀየር የጎንደር ከተማን የነዋሪነት መታወቂያ በመስጠት በሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ መተማ ከተማ ከዚያም ወደ ሱዳን ሊቢያ እንዲሁም ወደ አውሮፓ ለማጓጓዝ ጎንደር አውሮፕላን ማረፊያ እንዳሉ በቤተሰቦቻቸው ክትትል አማካኝነት ተደርሶባቸው ሳይሄዱ የቀሩ በመሆኑ ተከሳሽ በፈጸመዉ ሰውን ድንበር ማሻገር ወንጀል ተከሷል፡፡
ተከሳሹ ህጻን አብዱልሰላም ሙሀባ፣ ህጻን አብዱልናስር ቃሲም፣ ህጻን ዩኔ ቃሲም እና ህጻን አብዱርሃማን ሁሴን በተባሉ ልጆች ላይ ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት በመፈጸም በቀረበበት 5 ክስ በሶስቱ ጥፋተኛ ተብሏል።
በዚህም በ12 ዓመት እስራት እና በ8 ሺህ ብር ገንንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።
በመቅደስ ከበደ