የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ጥንታዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት እየተሰራ ነው

By Hailemaryam Tegegn

December 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ጥንታዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ፡፡

የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የቁጥጥርና አሠሪ ኮሚቴዎችና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በክልሉ የቅርስ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ምክክር እያደረገ ነው።

የቢሮው ኃላፊ መልካሙ ጸጋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ ለቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የእድሜ ጠገብ ቅርሶች፣ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶች እድሳትና ለቅርሶች ጥበቃ የሚያገለግሉ ሙዚየሞች ግንባታ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ጥንታዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ ለቅርሶች ጥገና የሚመደበውን በጀት በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡

የቅርሶች እድሳትና የሙዚየሞች ግንባታ ከብክነት በጸዳ መንገድ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የቁጥጥርና አሠሪ ኮሚቴዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ቢሮው አሳስቧል፡፡

የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራው ጥንታዊ ቅርሶች ለጉዳት ሳይጋለጡ ደረጃውን በጠበቀ ሙዚየም ለጎብኝዎችና ለአጥኝዎች በሚያመች መንገድ እንዲቀመጡ ያግዛል ነው የተባለው።

በክልሉ ከማኅበረሰቡ በተሰባሰበና ከክልሉ መንግሥት በተመደበ በጀት 30 ጥንታዊ ቅርሶችና 11 ሙዚየሞች በጥገናና በግንባታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ የክልሉ መንግሥት 111 ሚሊየን ብር ለቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ በጀት መመደቡ ተመላክቷል።

በሰሜን ጎንደር ዞን የምትገኘው ደቋ ኪዳነ ምህረት ገዳም፣ በሰሜን ሸዋ የሚገኘው የሸዋ ሮቢት ቦዜ መስጊድ፣ በደሴ ከተማ የሚገኘው መርሆ ግቢ ሙዚየም በጥገናና በግንባታ ላይ ከሚገኙት ቅርሶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በደሳለኝ ቢራራ