የሀገር ውስጥ ዜና

ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው

By Hailemaryam Tegegn

December 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመጪው ጥር ወር የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በጎንደር ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው፡፡

አቶ ቻላቸው ዳኛው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ወርሃ ጥር ለጎንደር ከተማ ልዩ መልኳ ነው ብለዋል፡፡

በዓለ ጥምቀትን በድምቀት ለማክበር ስምንት ኮሚቴዎች ተቋቁመው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፥ ከጥር 1 ጀምሮ የተለያዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከበርካታ ዓመታት በኋላ ጎንደር በልማት ስራዎች ገፅታዋ እየተቀየረ መሆኑን ገልጸው፥ ከሁለት ሚሊየን በላይ ህዝብ በበዓሉ ላይ እንዲታደም የከተማ አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል ነው ያሉት፡፡

የከተማዋን ታሪካዊነት በሚመጥን ሁኔታ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፥ የፋሲል አብያተ መንግስታት ከነበረበት የህልውና ችግር ወጥቶ በፌዴራል መንግስት እገዛ የቀደመ ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ታድሶ ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ የልማት ስራዎች የከተማዋን ገፅታ በመቀየር ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል በጎ ዕድል እንደሚፈጥሩ የተናገሩት ከንቲባው፥ ይህም የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያግዛል ነው ያሉት፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎችና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዓሉን ለማክበር ለሚመጡ ለእንግዶች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ የተጀመሩ ቀሪ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በፍጥነትና ጥራት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በምናለ አየነው