የሀገር ውስጥ ዜና

ጤና ሚኒስቴር በድሮን የታገዘ የክትባት ሥርጭት በይፋ ጀመረ

By sosina alemayehu

December 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማርበርግ ቫይረስ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሕይወት አድን መድኃኒቶችንና ክትባቶችን በድሮን የማድረስ ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

የጤና ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ነው በድሮን የታገዘውን የክትባት ሥርጭት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰነች ወረዳ ያስጀመሩት፡፡

መርሐ ግብሩ ሚኒስቴሩ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታትና ራቅ ያሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የወሰደው ፈጣን ምላሽ ርምጃ አካል ነው፡፡

በዚህ መሰረትም በዛሬው ዕለት በዳሰነች ወረዳ በድሮን የታገዘ የክትባት ሥርጭት በስኬት መከናወኑን ጤና ሚኒስቴር ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

የዳሰነች ወረዳ ካለው ራቅ ያለ መልክዓ ምድር አኳያ በመኪና ለማጓጓዝ ረጅም ሰዓታት ይወስድ የነበረውን ጉዞ በድሮን በመታገዝ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ክትባቱን ማዳረስ መቻሉ ተመላክቷል፡፡

ይህም ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ወረርሽኞችን ቀድሞ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅማቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገራቸውን በተግባር ያሳዩበት ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ወረርሽኞችን ለመመከት የራሷን የውስጥ አቅም እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠቀም መጀመሯን የሚያሳይ ትልቅ ተግባር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይም መሰል በድሮን መድኃኒት የማድረስ አገልግሎት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል፡፡